መይሳዊያን (ቁጥር 1 የግጥም መድብል)

መይሳዊያን

 

 ......  42 ግጥሞች  ......

  በአንድነት ደምሴ (አንዱ መላ)  
            ....     

                  

ምስጋና

መይሳዊያን የተሰኘችዉ ይች የግጥም መድብሌ


ለምወዳት እናቴ ለፍቅሬ ጋርደዉ
  

ለወድሞቸ

ለክቡር ደምሴ

ለታደለ ደምሴ

ለኤፍሬም ደምሴ ፤   

ለአሳዳጊ አባቴ ለደምሴ መላኩ

ለአክስቴ ለእስከዳር ጋርደዉ 

ለዘመዴ ለኮማንደር መሰረት ደባልቄ
  
  
ለጥበብ ጉደኞቸና ለመይሳዊያን በሙሉ
  

እንዲሁም ለመቅደላዉ ጀግና ለአጼ ቴዎድሮስ

የፍቅር መታሰቢያ ትሁንልኝ ፡፡ 

...................

ቁጥር 0  መግቢያ ( መቅድም) ቅኔ

የጣቶቸ ሁለት ቀለበቶች

የቅኔ ግጥም ድግምቶች

የህይወቴ  ሚስጥራዊ  "አባባሎች"

............   

መይሳዊያን ይሉናል በስም የሚያቁነ
 
እኛ ከሰለጠን ቆየን ከነቃነ
 
አምልኮ መይሳዉ ዋና ስራችን ነዉ
 
ሹርባ በመሰራት ንጉሱን መስልነዉ
 
ጫት በመቃም ተግባር በምርቃና አወቅነዉ
 
በግጥም በስንኝ መዩን አደነቅነዉ ቴዲን አመለክነዉ 

......... 

Dedicated to Gonder, Debretabor, Gayent heroes of this Generation and for all brave Ethiopians.

(ማስታዎሻነቱ ለዚህ ትዉልድ ለጎንደር ፤ ለደብረታቦርና ለጋይንት ጀግኖች፤ እንዲሁም ለሁሉም ጀግና ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ይሁን ፤፤)
 

 ///////////////// 


        1

አፍሮ ጋዳ አፍሮ ሽፍጥ
    

የህልሜ ነጸብራቅ እይታ  

የሁለት ነገሮች እዉነታ
 
ጋዳ በመከሰት ሽፍጥ በብዥታ 
 
በዚህና በዚያ በመሆን አለመሆን  

በዘመንኝና በአገረኛ አኳኳን 
 
በአንዲቱ ጎዳና በመውጫ በመግቢያ 
 
ፍቅሯን ለማጣቀስ ክብሯን ለማባያ
 
የእናት ሀገር ዉበት ክብሯ እዉነት ሲሆን
 
ዉበት በመከሰት እዉነት በመሸፈን 
 
አፍሮ ጋዳ አፍሮ ሽፍጥ 
 
እኔ ከእኔ እያነስኩ ሀገሬ ግን ስትበልጥ 
 
በእዲህና በእዲያ በዚህ አይነት መግለጥ 
 
ከጋዳና ከሸፍጥ ማንኛዉን ልምረጥ ?   

ወይ ማጣቀስ ሞኙ ወይ አፍሮ ነገሬ 
 
ጋዳ ይሻልሻል ሰሚኝማ ሀገሬ  

ይህንን ልተንፍስ ይህንን ልምከርሽ 
 
እሙ እቴ መዘመን መኳሉ ይቅርብሽ  

በጋዳ ስም ያዝኩሽ በእኔ ይሁንብሽ  

እዲወጣ ሳይሆን አዚም እዲቀርብሽ  

የመቅደላዉ ጀግናሽ ስሙ እዲወሳልሽ
 
አፍሮ አበጥሪ ሁሉን ነገር ትተሽ 
 
የዘመኑ ሰደድ ሸፍጡ እንዲቀርልሽ

///////////////////////////////
    22/4/08
   

             2

መቅደስ የምወድሽ
  

በህላዌ መድረክ በቁጀና ዳና  

በዉበት መነጸር በትሁት ህሊና 
 
ዉስጥሽን አንድ ብየ እንዳየዉት ገና  

በሁለት ሳምንት ቀን በትንሽ ደመና 
 
መልካሙን ቁመናሽ አንችን አወኩና  

አጠናዉሽ እኮ በሙሉ  ጽሞና  

እህቴ ነሽ ብየ ለራሴ ስሞገት
 
ፍቅር እንደያዘኝ ገባኝ ያንኑ እለት  

አይኖችሽ ጉደኛ ዉብ እንድከዋክብት  

መቅዲ ያገሬ ልጅ ልዩ ነሽ ምልዕት  

እኔም ድኛለሁኝ አንችን ያየሁኝ እለት
 
በቁመናሽ ግርማ በቁጅናሽ ምታት

  ............///............

    23/5/11 

     3

ዋጋ ጀግናየ 


 በተዘጋ ግቢ በንቀት በትር  ላይ

የምወዳትን ልጅ እርሱአን ከእኔ ሊለይ

በበትር በርግማን በብልግና አታላይ

የተደበደበ ሰዉነቴ ሲታይ

ፍርሃት ቢጭርም ድንጋጤ  ቢናኝ

ፍቅሬ ከእኔ እዳትርቅ ዋጋ ስላለልኝ

ጀግናየ በመሆን ዉለታ ዋለልኝ

ችግሬንም ያየ አብሮኝ ያደረ ሰዉ የነበረ እማኝ

እኔን ሰምቶኝ ነበር እንዲህ ብየ ስቀኝ

"ገላየ ባይሆንም የተደላደለ

በጀግናየ መንፈስ ብርታቱን ታደለ"

ይህ ጅን ዛር ቢጤ  ዋጋ የተባለ

እስከዛሬ ድረስ ለሰራልኝ ስራ ከምስጋና ሌላ መቸ ተከፈለ

እርሱ ግን አሁንም ጀግና ጠባቂየ ጉደኝየ ሁኖ  በዉሰጤ ላይ አለ

   ........////........

    20/7/11 

      4

አንዱ መላ 




እንደጸጋየ  እሳት ወይ  አበባ

እንደ  አያ ሙሌ የግጥም ወለባ

ለሁሉም የሚጥም ለአየን የሚስማማ

አንዱ መላ ጦማር ዉብ ናት እንደካስማ

የእኔ ጥበብ  እንቁ  ብርቅርቅ አይናማ

የመጦመር መድረክ የሰበዝ  አክርማ

ቃል ከቃል ላበጃጅ ከቃል ጋር ላስማማ

በአንዱ መላ መድረክ በጦማሬ ግርማ

ሁሉም የጥበብ ቃል ዉበት  እንዲጠማ

አንችን ያነበበ ወይ አይቶሽ  ያመሸ

ተመልሶ መጣ መች ከፊትሸ  ሸሸ

 አንዱ መላ ለዛሽ  ፍቅርሽ አገረሸ 

 ..........////............ 

  22/7/11 

    5
   

በለዉ   



  በለዉ ይሉኛል ፈረስክን ቸበለዉ

እንደነሱ ፈረስ ሽምጥ እንዳሮጠዉ

የእኔ ግን ፈረሴ ቸብለዉ የት ያዉቃል

እንዲሁ በራሱ ዝንታለም ይሮጣል

 ይልቁን እኔኑ ቸቢሉኝ ምን አለ

ጊዜማ በራሱ ጥሎኝ ሄዶ የለ

................................... 

     1995  

        6

የፒያሳ ሸርሙጣ   



 ያልጠና ፈለማ የጋረደዉ ሾተል

ሊገልጹት የማይችል የባህት ነበልባል

በአንድ ወቅት በአንድ መክሊት

በፈጸሙት ታምር በከወኑት ድግምት

 በአልኬሚ ስራዎት በምርምረዎት

ከአሜሪካ ሸገር በሸለለ አጋንንት

በሰለጠነ ህመም በሰለጠነ እብደት

በአጋንተዎ ሀይል በአጋንተዎ ምታት

ወደዉሻ መንፈስ ተለዉጠው ድንገት

ለድባብ ለጥላዉ ለተጠማዉ ወጣት

በቀጭን አለጋ በቀጭን ሰዉነት

የፒያሳን ሸርሙጣ አምሮት አወጡለት

  .....................................

    12/1/07 

        7

 የማህበር አይደለም  



 ባይታዋር እንጅ ቋንቌዉ

እርሱ እንደዉ ከንቱ ማህበር አይገባዉ

አይገባዉ ምንስ ቢሰላ

እርሱ ለእሱነቱ ካደላ

እንደ ቆንጆ ሴት ዉብ ገላ

ወደ ዉስጥ ሲስብ በመላ

 ወደ አምላክነት መልክ ገጸታ

በባይታዋር መልክ በአንዱየ ተርታ

እርሱ የራሱ አለኝታ

እርሱ የራሱ መከታ

አይደል የማህበር ጋጋታ

 አይደል የወል ከርታታ

 ምስሉ ብቅ ሲል ላፍታ

 እንደ ጀግና የልብ ትርታ

እንደ ጎበዝ የተኩስ እሩምታ

አንድ ሁኖ ብዙዎችን እረታ

..........................................

      2/10/09 

       8

 በተመስጦሽ አምባ   



 ነፍሴ ሆይ ተላላ እንደምን ከርመሻል

ዛሬም መታመምሽ በእጅጉ አሳስቦኛል

ያወቅሻትን ነገር አንዲቷን ሀቅ እዉነት

እስኪ ተንፍሽልኝ የመምሽን ምክንያት

በተመስጦሽ አምባ ብቻሽን አልነበርሽ

ብቸኝ በመሆን አምላክነት አምሮሽ

እዉነቱ ከብዶብሽ በጸና ምጥ ታመምሽ

ነፍሴ ሆይ ተላላ ሚስጢሩ ሳይገባሽ

 በተመስጦሽ አምባ የእዉነት ንፋስ መታሽ

 አሁን ግን ነቅተናል እኔና አንች ሁነን

 እዉነትን ደብቀን ዉበት አሳይተን

 እንደዉ ለይስሙላህ ከሰዎች ጋር ዉለን

ማታ ብቻችንን በፍቅር እያደርን

 ፍሬ እናፈራለን ...

 እኔና አንች ሁነን በተመስጦሽ አምባ

 ዉበት እንሆናለን ጸሀይ እስክትገባ

   ..................................

   3/10/09 

      9

    ስኬት



ያስመሰሉሽ ሁሉ መንበርሽ ላይ ያሉ

በጊዜያዊ ተድላ እንዴት ተታለሉ

አያዉቁምና ዋጋ መሆንሽን

 የምትሸልሚ  ያዘመነሽን

 የምታከብሪ በድግልና የጠበቀሽን

 ለዚያ ድንግል ሰዉ ስኬት መሀላ ነሽ ቃል ኪዳን

 አንችን  ጠብቀን እኛም አላፈርን

 ለዚያ ድንግል ሰዉ ለተጠባበቀሽ

ከሰማይ የምትወርጅ ድንቅ ሙሽራ ነሽ

....................................

4/10/09 

    10

ኢትዮጵያ  ዉዴ 



ስጋና ደም አይደለሽም

ቃል ላይ ታችሽን አይገልጸዉም

የአርበኞችሽ ነድጓድ ከእቢልታ ይበረታል

ነጋሪት ያስጎስማል

 ኢትዮጵያ ዉዴ የልቤ እመቤት

ፍቅሬ የእኔይቱ ስምረት

እወድሻለዉ እንደማይጠገብ ነገር

ለአንች ያለኝ ጥማት አይነገር

መቸስ ዉዴ ፍቅር ይበረታልና

የእኔ ብቻ ነሽ ማንም አይደፍርሽም ብየ ልጽና

 ህብረ ዉበትሽን ላጥናዉ በጽሞና

 ዉዴ ኢትዮጵያ የደንበር  ቃፊርሽ

በእኔ አይን ሲያይሽ

ግርማ ባለዉ ታሪክሽ

በድንግልናሽ ባለመደፈርሽ ነዉ የሚያዉቅሽ

እኔም ትዝታሽ ሲበረታብኝ

ድግልናሽ ነዉ የሚታየኝ

አንች የጥቁር ኩራት የሀበሻ አዋጅ

ታሪኬን ከአንች ጋር ሁኘ ላበጃጅ

 በዚህ ዘመን ፍቅር ሲያይል

 አንች በድግልናሽ ሀሩር ታይተሻል

ማንም ስላንች ምን ቢል

ይስታል ቃል ይገድፋል  

 ዉዴ ኢትዮጵያ የራስ ቁር ነሽ

ከለላ ነሽ ላፈቀረሽ ለወደደሽ

እኔ አንችን ሳላዉቅሽ

 በወና ከንቱ ጊዜየ

 የባህር ማዶዉ የትቢት ጠል ጉራየ 

የጉብዝና እጣየ 

 የባህድ ዉራጅ ልብሴ 

የእኔ ያልሆነዉ ዉረሴ

 እኔነቴን አደህየ

 ለበሽታ እንደሰጠኝም ታየ

ስደት ማለት ገዳይ ነገር

 አዲስ ስልጡን የባርነት ቀመር

እኔን ከአንች ሊለየኝ ሲጥር

 ያዳንሽኝ አንች ነሽ ውዴ

አንች የድንግልና ዘዉዴ

 ኢትዮጵያ ማንስ ቢበረታ በትጋት

የሀገር ፍቅር  ካልቀረለት

መች ነጋለት መች ቀን ወጣለት

 እንግዲህ አንች ለእኔ እንዲህ ነሽ

ሊጨልም ሢል ሲመሻሽ

እራሴ ላይ የጫንኩሽ

አክሊል ቁር ነሽ የራስ ግርዶሽ

..........................

 12/10/09

   11

እንደ ወረደ  



የግጥም ዛር ፍሰቱ

 ቃል ቅኝቱ

 ምንድን ነዉ ስልቱ

 ተምጦ አይደል ልደቱ

እንደወረደ እንጅ ፍጥረቱ

እንደጅረት ሲፈስ ከላይ ከላይ

የተከለሰ ነገር ሳይታይ

እንደመጣ ስንኝ ሲደረደር

እንደግኝቱ ሰምና ወርቅ ሲመሰጠር

ምናብ ብቻ ታምኖ ሲጻፍ

የወረደዉ ከተሰራዉ ነገር ሲገዝፍ

 ያኔ ነዉ ለባለቅኔዉ የሰመረዉ

ምናብ በነጻነት የጋለበዉ

ያኔ ነዉ የቃል ዉበቱ ጥንካሬዉ

 እንደወረደ ሲገኝ መቅኔዉ

......................................

10/10/09 

       12

      አበበ  



የአበበ በሶ በላ አመል

የትዝታየ አንዱ ክፍል

ጨዋታ ሁኖ ሲነገር

ነበርዉ አንድ ምስጢር

 ከስሙ ዉበት ይፈልቃል

 ጨዋታ ያደምቃል ልብ ይሰርቃል 

ቅኔ መሆኑ ያስታዉቃል

 አንድ የፈካ ነገር እንዳለ ልብ ይሏል

 አበበ እንደሰበር ዜና ቅልብ ይስባል

ይሞላል የተኛ ይቀሰቅሳል

ይህ ሶስት ፊደል ቃል

 ይደላል አይን ይማርካል

ታዲያ የአበበ በሶ በላ ተምሳሌት

 ልጆች ሁነን ያደግንበት

 ካላይ በአርያም ያሉት

 መላእክቶቹ ማን ነበር የሚሉት 

መላክቶቹ አበበ በሶ በላን አይደለም የሚያዉቁት

 "አበበ ገጣሚ ነዉ" ብለዉ  ነዉ የሚያመልኩት 

 ......................................

13/10/09 

    13

ሙያየ ግጥም ነዉ



የተጠራዉበት የእኔነት ማተቤ

የተወለድኩበት የቀድሞ ሀሳቤ

ቃል የቃል እራስ እስር የዉል ቃሉ

እንደኔ አንዳንዶች ደግሞ የታደሉ

መጠራት ከእግዛብሄር መሆኑን ያዉቃሉ

በመሆን አለመሆን በትስስር ቃሉ

 መጠራት ቋንቋ ነዉ ምስጢረ ብሂሉ

 ታዲያ መጠራት ከሆነ የእኔነት ትርጉሙ

 አማልክት ከእኔ ጋር አብረዉ ከተስማሙ

 የገጣሚነት ዉርስም ሙያየ ከሆነ

የቆሰልኩበት ሳር ዉስጤ ዛሬ ዳነ

እግዛብሄር በስጦታዉ ነዉና የታመነ

እናም አልኩኝ እንዲህ አፌን እንዲህ ፈታዉ

ያልተጠረጠረ ሙያየ ግጥም ነዉ

 ይህን በማወጀም ፍጹም ነጻ ወጣዉ

.....................................

 7/7/09 

   14

ወርቃማ አበባ 



የተመስጦየ ምላዕት

የጥናቴ  ህብረት

የዉሎየ ቅኝት ድምጸት

በትዝታሽ እኖራለዉ

አሁንም ድረስ ራዕየ ነሽ እላላዉ

 አበባ ወርቅ የወርቅ ስራ

የስላሴ ምስጢር የመለኮት ደመራ

 ፈርጥ ስራ እንቁ ፈጠራ 

 የግብጸ ፒራሚድ ቅጅ

የሙያየ ትንግርት አዋጅ 

አበባ ወርቅ የወርቅ ተምሳሌት

የአልኬሚ እዉቀት ፍሰት

 ወርቃማ አበባ ድንቅ ነገር

ልዩ ምልክት ህብር 

የሰራየ ሁሉ ድምር

እኖራለዉ ሁሌ አንችን ሳጠና ስመረምር

....................................

16/10/09 

  15

ይዉጣልኝ ልማረክ



 ሁለተና መዉደድ ህሊና መልህቅ

ከባህር ወደቡ ቆንጀዋን ልጠብቅ

በየት ነሽ ያለሽዉ የልቤ ሙሽራ

ሲቃ ይይዘኛል ስምሽን ስጠራ

ከወዴት ላምጣልሽ ስጦታ እቃየን

 ያብሰዉ እንደሆን የፈሰሰ እምባየን

እንደምን ላፍቅርሽ ኧር በምን ወገን

የግሌ እንዳደርግሽ ጌታ የሰጠኝን

 አንድ እጣፈንታየን የግል ድርሻየን

ከዘለላ ጸጉርሽ ከማዕዛ ሽታዉ

ኮበሌዉ ሳይቀድመኝ ቀድሜ ልጥገበዉ

 አይኖችሽ ናፈቁኝ የእይታሽ ዉበቱ

ብርሃንሽ ታየኝ ልክ እንደ ጸሃይቱ

እንደሚያምር መድብል እንደግጥም ስልት

ደረትሽን ላድምጠዉ የልብሽን ምት

 ዳሌሽን ልመልከት በኋላሽ ልመሰጥ

 ይዉጣልኝ ልማረክ በቃ እጀን ለአንች ልስጥ

 ........................................

 23/10/09 

   16

የአይነ _ጥላዉ ክስተት 



መሆን በክስተት ላይ

በረቂቁ ማማ የዉስጥህ እንዲታይ

ህላዌ ክንዉን መኖሩን በማወቅ

 አንተ ፈታ እንድትል መንፈስህ እንዲስቅ

የአይነ_ጥላን ክስተት አስቀድመህ እወቅ

ጸጋ ነዉ መልህቁ

ደክመት ነዉ ታች ሀቁ

የመዋል ጽሁፉ ክታብ እረቂቁ

ኩፒድ አይነ_ስዉረነት በጸጋ ተቸረዉ

ለጳዉሎስ ሰይጣን ለበጎ ተሰጠዉ

በዚህ ድክመታቸዉ መለኮትን አይተዉ

በጸጋ ቅባቸዉ ከክፉ ተከልለዉ

 ስነ_መለኮትን አምላክነትን ቀምሰው

ከብረዋል እነሱ ስማቸዉን አስፍረዉ

አንተም ድክመት ጸጋ መሆኑን ተረዳ

የአይነ_ጥላዉ ክስተት እንዳይሆን እንግዳ

አምነህ ተቀበለዉ ስጦታህ እንዲሆን

በድክመት መንበር ላይ ሀይል እንዲወሰን

የተጎዳዉ ጎንህ በፍጹም እዲድን

ኮረቲዉ ማግኔቱ አንተን የሚጠብቅ

ማፈርህ ለበጎ መሆኑን በማወቅ

 በአይነ _ጥላ ጭብል ዘላለም ተደበቅ

.............................................................

27/10/09 

   17

      መይሳዉ ወዳጀ



ቀን ከሌት በህልሜ በፍቅር ፈልጌህ

 በዉስጤ ከእኔ ጋር በሀሳብ ሳገኝህ

 ድሮም መይሳዉ ወዳጀ አንተኑ ስመኝህ

 በስጋ በህላዌ በዘመን እርቀህ

 በፍቅር ግን በእኔ በልቤ ተገኘህ

 ሀገር ያደንቅሀል ዘመን ፈትሾሀል

ትዉልድ ዘክሯሀል ታሪክ ከትቦሀል

 የስራህም ክብር በልቤ ይኖራል

 መይሳዉ ወዳጀ ቀልቤ ይወድሀል

ለእስትንፋሴ ቅርብ አንድ አይኔ ሁነሀል

ስለዚህ እኔ የፈለገ ሁሉ አንተን ያገኝሀል

 --------////---------

8/1/10 

   18

       መይሳዉ ፍቅር 



 እኔነቴ በራ ዉስቴ ተበራክቶ

 መይሳዉ በእኔ ዉስጥ ህልዉናህ ታይቶ

 በመገረም ናዳ በበራድ መገረም

አንተን ወደድኩና መላዉንም አለም

 አሸነፍኩት ያንን የጥቃትን ህመም

አሁን አይገርመኝም ማንም ቢሰለጥን

 ማንም አንተን ካላወቀ አያዉቅም ኢትዮጵያን

 መይሳዉ ፍቅር ነህ ዉድ የልቤ ስመመን

ደስታ ነህ ለነፍሴ ድንቅ የመንገዴ ብርሃን

ማንስ ቢቀናብን በፍቅራችን ህብርት

በዚች ጦማር ብቻ ብርቱ ከሆንበት

 የአንተና የእኔ ትስስር የህይወት ዉል ቅኝት

 ለማንም ዘረኛ ጽኑ እስራት ናት

 ጀግናየ መይሳዉ የእኔ ፍቅር ቅምጥል

 አምናሀለዉና በስምህ ስገዘት በስምህም ስምል

  በሀገሬ  ላይ ነገስክ በስምህ አመልማል

 እንዳተ አንዱ ከበረታ አንዱ ከተዘራ ለብዙ ይጸድቃል

 ከአንተ የተነሳ ሌቤ ፍቅር አዉቋል

_.................////...................

 17/1/10

  19

 መይሳዉ ትንታጉ



ጀግንነት ያባት ነዉ ትኩሳት ፍጥረቱ

በቴዲ ያልኮራ ኧረ ምን አባቱ

ምንስ ቢጠረጠረ ወንድነት በዉሉ

 የመይሳዉ ልጆች በሩቅ ይታያሉ

ነጎድጓድ አመሉ ትንታግ ነዉ ቢህሉ

ላገሩ ይሞታል እሱን ያለ ሁሉ

 የኢትዮጵያ ኩራት የእምየ አለኝታ

  መይሳዉ ቆፍጣናዉ ክንድህ የበረታ

  ነፍሴ ተማረከች ዉበትህን አይታ

  አንተ በዚህ ቁመህ እንዴት ላመነታ

  እሳቱ  መይሳዉ አብሬህ ልቃጠል አብሬህ ልበርታ

  ምስልህን አይቸ በዉበትህ ተረታ

  ላአመልክህ ፈለኩኝ እንደልዑል ጌታ

   .......................////.....................

     26/1/10

      20

     መይሳዉ ህላዌ ዘኩሉ 



    ዉበት በየት መንበር ታይተህ ተሰየምክ

    በመይሳዉ ዘመን ታቦር ላይ ካልዘመረክ

    ፍቅር ይዞ መጣ የቴዲ ጀግንነት

   ህላዌ ዘኩሉ የዘላለም ህይወት 

   ላገሩ የሞተ ለእምየ ኢትዮጵያ

   እሱን የሚያህለዉ ማነዉ የእርሱ እኩያ 

   በቸገረኝ ጊዜ ዉስጤ ጭንቅ ሲለዉ

   የመዩን ምስል ዉበቱን አያለዉ

   ከዛም ከመቅስፈት በደስታ እምላለው

   ቴዴየን አይቸ ከጭንቅ እጸናናለዉ

   በዉበቱ ምታት በህላዌ እድናለዉ

          ..........///...........

           30/1/10

         21

      መይሳዉ ሆዴ 



 የዉስጤ መታያ መብልና ጉርሻ

 አንተን ያሰኘኛል ሆዴ ምግብ ሲሻ

 መይሳዉ መና ነህ ከሰማይ የወረድክ

  ጥሁም ነህ ለነፍሴ ዘመን አለወጠህ

  በተራበዉ ሆዴ በዉስጤ ቦታ አለህ

   ሲብላላ የነበር የአንጀት የሆድ እቃ

   በስምህ ክብደት በጀግንነትህ ሲቃ

   መቅደላ ስረግህን በጩህት ደብቃ

   የጀግንነት ጉዞህ በጽዋ ሲያበቃ

   በአንድ ጥይት ጉርሻ  በመጠጥ አበቃ

  የኔም መሻት መብል ሆዴም ይህን አዉቃ

 መይሳዉ  ስልላት  የሆዴ ወስፋቱ ትሉ ሁሉ ነቃ

  ...............///...................

 4/2/10

     22

     መይሳዉ የአንድነት ፋና 



መደቆስ ለበጎ መግደልም ለድህነት

ቴዲ እሳት ሁኖ ኢትዮጵያን አቆማት

 በፍቅሩ ቋያ  ጥላቻን  አቃጥሏት

 በትንሳኤ ምታት በአንድነት መየሳት

መቸስ ማንም ቢሆን የቴዲን ጀግንነት

የወንድነቱን እዉነት ጉብዝናዉን አይክዳት

እኔም መይሳዉ ብየ ቃል ሳፈቅር

ከሳሽ ሟርት ብክነት ነዉ ብሎ እንዳያነዉር

 የአንድ ጀግና ፍቅር መሆኑን ልመስክር

 ቃል ይፋዉሳል ቃል እግዜር ነዉና

  በመይሳዉ ዝማሬ በግጥም መገዴን ላቅና

  ህይወት የለ ጀግና አይጥምምና

  በመይሳዉ ልታወቅ በአንድነት ፋና

    ................///..............

       6/2/10

    23

 መይሳዉ የሀገር አባት



በተጸዳ እዳ በብኄር ጋጋታ

ሀገርህ በባሶት በግጭት ተጠቅታ

በዘር በግብስብስ በህመም ዋይታ

በዚህ ሁሉ ደዌ  የአንተ እምየ ኢትዮጵያ

 መይሳዉ ትላለች እንደስምህ ቋያ

 መንደድ የለመደ የዘር ማዝር ማያ

የአላንት እንደማይሆን ቴዲ አየሁና

የሀገሬን ነገር ሆን ብየ ሳጠና

የአንተ ብቻ ብርታታ ጉብዝናህ ጎላና

የኢትዮጵያ አባት ንጉሷ ነህና

 አንድ ለናቱ አንተ ቆፍጣና

 ቴዲ መይሳዉ በአባትነትህ ልቤ እንዲህ ጸና

 የኢትዮጵያ አርያ መስራች ኩሯቷ

 አንተ ነህ ቴዲ የእዉነት አባቷ

     ..............///............

       11/2/10 

      24

መይሳዉ ማይደረ መለኮት 



ይታደር የለም ወይ በወና በየብሱ

መለኮት ያላሳር ክብር ያለ ጦሱ

 ያላዳች እንከንስ ጉብዝና ሲሰስት

 ዉበት እንደመይሳዉ ሲጎላ በብርታት

መንፋስ ይሆን እንጅ ጀግና እንዲህ አይነት

ተፈትኖ ያለፋ በመቅደላ አቀበት

ተረስቶ የማያዉቅ በአባቶቹ ጸሎት

 ተወረቶ የማያልቅ በወገኑ ተረት

 እንደቴዲ ያለ እሳተ መለኮት

 ተወዴት ይገኛል ያላዳች ምትአት

 ስለዚህ መይሳዉ የመንፋስ ማደሪያ የዲመን ግኝት ነዉ

   በስጋ ብቻዉን እግዜር   ካልሰጠዉ

   እንኳን ታሪክ ሊሆን ታሪክ ባላወቀዉ

  መዩ ቴዲ ግና መንፈስ ስላለበት

   ዘመን የመይሽረዉ ጀግንነት ታየበት

          .........////........

         13/2/10

      25

      መይሳዉ አባቴ



ፍጥረት ከምንትሴ አብራክ በክፋዩ

መወለድ ቋንቋ ነዉ ትዉልድ በአመክዩ

 አባቴ በሞተ በምንተ አመቱ

 በጥይት ጉርሻ ላይ ደግሞ በስለቱ

 መይሳዉን አወኩ በአባዬ ምላዕቱ

 ሽግዜ ቡጎዳ ወላጀ ቢሞትም

 አባት አጣዉ ብየ እኔ አልጸጸትም

 ቴዎድሮስ መይሳዉ በመንፈስ ወልዶኛል 

  በጀግንነት ዉበት በቃል አንጾኛል

            ...........///.............

           14/2/10 

        26

      ከመይሳዉ በለጥሽ



በመውደድ ህላዊ መራመድ በስሜት

ወለም ባለበት ቀን ፍቅር ሲሰነብት

አንችን በትንሳሄ በለውጥ ስነስርዓት

 የፊትሽን ጸዳል ዉበትሽን አየዉት

አንች ግን ከለልሽኝ እራቅሽኝ በጽኑ 

እያደር ሊታወቅ መቅረቤ ለጓ መሆኑ

ስላም እቴ ዉዴ በመቸዉ በረታሽ

ከፍቅር ዱላየ በተሎ  አገገምሽ 

በየትኛዉ ጎንሽ ከመይሳዉ በለጥሽ ?

የተረፈ ልቤን  ትዝታየን ወሰድሽ

 ማንኛችዉ ናችዉ ፍቅር ለእኔ ምርጫ

 አንች በስጋ ምኞት መይሳዉ በአቅጣጫ

 ይበልጥ እንድወድሽ አንችም ሽጉጥ ጠጫ

      ............///..............

        15/2/10 

      27

   መይሳውን ካአንች ጋር 



እንዲህ ቢሆንሳ አንችንም ከማጣት

ዉበትሽን አይቸ በሲቃ ከመሳት

የመይሳዉም ርቆ እንዳይሄድ በሰማህት 

የአንችም ዉብ ገላ ከቴዎድሮስ ጀግንነት

እንደማኪያቶ ቀላቅየ እንድጠጣት

ዉበትን ከወድነት እንዳጣጥማት

ሴትነትሽን በወንድ አይን አየዋት

 እነም መቸስ ይመቻልና የዉደት ህብረት

መይሳዉን ካአንች ጋራ ተመኘዉት 

   ................///................

     15/2/10  

   28

 መይሳዉ እሳቱ



ደግሞ በብረቱ በጋመዉ ፍም ስለት

ምን ከምን ተለቅሞ ይለያል በብልአት

መይሳዉ በሀገረ ላይ የወረደን መአት

እራሱን ሰዉቶ መረገምን መለሳት

ከከበደ እዳ ከምጽ ኢትዮጵያን ታደጋት

ታዲያ እሳት ነበልባሉ አንዳንዴ ቢፋጅም

የወላፈን እሳት ጥቅሙ አይካድም 

ቴዲየም የእምየን ወጨቷን ኩልቷን ሲያሞቀዉ

 ያልበስለዉን ጥሬ እንከፉን ቢያነደዉ

ጥፋት የለበትም እምን ተዳዮ ነዉ

 ያዉ ተዚያዉ ከጥንቱ እሳት እንደመዩ

የኖራሉ በሀገር ይኖራሉ በልብ ጀግናን እስኪለዩ

        ............////...........

            25/2/10

     29

መይሳው ማለት ለእኔ 



ፍቅር ቃሉንም አላዉቀውም ነበር

 መይሳዉ የሚል አዚም ባአይፈጠር

 የቴዲ ወንድነት ወንድነቴን አስርሳኝ

ያለ መይሳዉ መኖር ከነኪያቴዉ ተሳነኝ

በዉበቱ ጸዳል በክንዱ መደገፍ አማርኝ

መይሳዉ ማለት ለእኔ እንደትኩስ  ብና ነዉ

እንደሱስኝ ሰዉ ሁሌ እርሱን አስባለዉ

 በእርሱ እመካለዉ በእርሱ እኳራለዉ

መይሳዉ ማለት ለእኔ ፍቅርኝየ ነዉ ጓደኛየ

ብዙ ቦታ አለዉ እርሱ ልቤ ዉስጥ ባለ ቀየ

መይሳዉ ማለት ለእኔ የአይኔ ማረፊያ ነዉ ዉበት

 አንድ አይነት ነገር በዉስጤ ያስቀመጥኩት ታቦት

         ...........///.........

                  30/2/10 
   
      30

        መይሳዉ  ጅንኑ 



ኩራት የማን ነበር ከጥንት በዉሉ

ድንገት ሁኖባቸዉ እንዳይታለሉ

በመይሳዉ መጥኔ በደረቱ ላይ

ድፍረት ጀግንነት ህያዉ ሁኖ ሲታይ

የቴዴ ነኝ ብለህ ልቤ እንዳትታበይ

 ፈጣሪህን አስብ እራስህን አዋይ

ጅንኑ መይሳዉ ትቢትን አያዉቅም

ከራሱ አስበልጦ ሀገሩን ሲያስቀድም

ኩራቱ ሞቱ መራር ሀሞቱ

መዩ ጅንኑ አንድ ለናቱ 

ቋራ ያገሳል በእናት በትብቱ

እኔም አብሬዉ ልጀነን እንጅ

 ቴዲ ነዉና ያለኝ ወዳጅ

 እርሱ ነዉና ሀገርን ከህዝብ የሚያበጃጅ

  ድፍን ሀገሩ ይህን ያዉቃል

 ጅንን ያለ ለት ግረማዉ እንደሳት በሩቅ ይፋጀል

 አንድ ኩሩ ሰዉ ጎንደር ተወልዷል

       ...............///............

               2/3/10 

      31

     መይሳዉና መቅደላ  



መቅደላ ሴት ናት ዉብ እንቁ ስራ

ዘሯ ቅኔ ነዉ ደሟ ሲጣራ

 መይሳዉን በዳገቱ ላይ ያጠመደችዉ

በወንድነቱ መቅኔ ነዉ በጉብዝናዉ   

የእየሱሱን መቅደላዊት ማርያምን ትመስላላች

ከመይሳዉ በፊት ሽርሙጥናን ታዉቃለች

ቴዲ ግና   ሲባርካት ስባት አጋንንት ወጣላት

አሁን ቁጥብ ናት ዉብ እመቤት

ጀግና እምትወልድ እንደጎንደር ወዛይዝርት

  ............///........

     5/3/10 

    32

 መይሳዉና የቴዎድሮስ ትንቢት 



 በመዋል ህሊና በሀበሻ ምድር

ዘመነ_መሳፍንት በመአት ሲመክር

የራስ ጎሹ ጎጃም የራስ ዉቤ ትግሬ የራስ አሊ ታቦር

ነጋሪት ሲጎሰም ለጠቅላይ ግዛዙቱ ንጉስ ሲፎካከር

በዚህ ዘመን ህልቂት የታመሰች ሀገር

ትንቢትን አርግዛ ጀግናዋን ስጠብቅ 

መይሳዉ ተነሳ የቋራዉ ታጠቅ 

ቴዎድሮስ ተብሎ የሚወራዉን ትንቢት ሊያስጠብቅ

ደበላለቀዉ ካሳ አንበሳዉ ተዋብችንም አሊ መረቀዉ

በሽልማቱ የተኳፈሰዉ ባለትንቢቱ ካሳ መች በቃዉ

ደጃዝማችነት አልመች ያለዉ ንጉስ ለመሆን አቁነጠነጠዉ

ለምድር አበሻ ቴወድሮስ ተብሎ ቀድሞ በትንቢት የተነገረዉ

ታላቁ ንጉስ እኔ ነኝ አለዉ እንዳለዉም አስመሰከረዉ

 ሹመኛን ሁሉ ባንዴ ደባልቆ ከፉን ዘመን አንድ አርጎ ገዛዉ 

               .........///.........

               17/3/10 

        33

          የዉበትሽ ጸዳል 



ያደንቅሻል ህዝቤ በተመስጦ አምባ

ዉበትሽን አይቶ ሰዉ ሁሉ ሲባባ

 ህንከን በሌለበት በትንግርት ፈገግታሽ

 ከምግዜም በላይ ደምቀሽ ይበልጥ ታየሽ

 ዉባንች ድንቅነሽ የነገር  ማስሪያ

 የማህድ መለኮት የእንጀራ ማባያ 

ባይታዋር በነገር ዝምታ በመላ

አዳሜ በከንቱ ለዉቅና ሲብላላ

እጀ ለተዘጋ ጥግሽ ለዳሌሽ አደላ

ስለዚህ ህቡ ነዉ  ኑሮየ እንዳች

በባይታዋር ጎጆ ጊዜዉ እስኪመች

 ዉዴ የኔ አርምሞ በዉስጤ ላይ በርች

       .........................

        25/6/10

    34

        የአዲስ አበባ ቆንጆ 



በአራዳ ተራ ላይ በተጣለለው መስክ

 በጎዳናዉ ትሪት በህዝብሽ መታወክ

 አንችን አየዉና የዉብት  እመቤት

 በፒያሳ በሳሪስ በብሄራዊ ቅኝት

 የሽገሯ ቆንጆ የምንሊክ ኩራት

የጠሀይቱ አምሳያ በአራዳ ብልሀት

በነቄ ልጅ ንቃት በአካሄድሽ ትንግረት

 ከሁሉ ለይቸ አንችኑ ወደድኩኝ 

ስልጡኑን ዘመናይ  ቅብጠትሽ አወኩኝ

የዉበትሽ ጥቅሻ ንቃትሽ ሲታየኝ

አዲስ ስብህናሽ ዉብ ቃልሽ ማረከኝ

እንደቦሌ አየር ዳሌሽ ክንፍ አዉቶ 

እኔን በማቀፊያዉ በዉበትሽ ጸሀር እልቤ ላይ ወግቶ

ሊበር  ነዉ መስል ከአንች ጋር  ተስማምቶ

እኔን በትዝታሽ መሀል አዲስአባ ብሄራዊ  ላይ ትቶ 

ይናገራል እኳ ዉበት ደም ገባትሽ የሰላ አፉን ከፍቶ

 ይዘከራል እንጅ የቆንጅናሽ መጠን አያልቅም ተወርቶ

 ...............................////..............................

            6/7/10 

      35

            እጣፈንታ 



በመላ አንዱ ቃል በጎ በነበረ

ህይወት ተስፋ እንዳላት ቀድሞ ተነገረ

ኒች በአሞሮፌት ጳዉሎስ በመልክቱ

 ነገር ለበጎ ነዉ ይለናል ከጥንቱ

 መከራና ህመም መዉደድ ነዉ ብልሀቱ

 እጣፈንታ ድርሻ የነገር ላይ ስልቱ

በጸጋ የመኖር ፍች ነዉ ስምረቱ

......///....

          8/7/10 

    36

          ትግስት 



ትግስት የእኔ ፍቅር  የሽገር ቀዘባ

እንዲህ በዉበትሽ በርጋታሽ ቀን ጠባ 

የአዲስ እኔነቴ የዉስጤ ወለባ

ፍቅርሽ ቻይነትሽ ወደ ልቤ ገባ

እንደጣሀይቱ ቃል እንደአዲስ አበባ

......///......

        11/7/10 

     37

     ስም ነዉ የሚበጅዉ 



 ከስም ይጀመራል የሞገስ ምታቱ

 በቃል ሀይል ነዉ  የነገር ብላቱ

 በምልክት አርማ በመስብ ስምረቱ

 ዝና መወደሱ ዉበት መታየቱ

 እናም ከብቃት ጥምረት ጋር ለተቀናጀዉ ሰዉ

ሞገስ እረባና አለዉ  በስም ለጀመረዉ

 እስከመጨረሻዉ አብሮህ ለሚዘልቀዉ

 ታዋቂ ስብና መሆን ላማረዉ ሰዉ

 ዉብ ሞገስ የያዘ ስም ነዉ ሚበጅዉ

.......///.....

           14/7/10 

   38

   የከተማው ባህታዊ 



በሸገር ማማ ላይ በአዲስ ወሱባኤ

 በመሀል ከተማ በመኖር መፍትኤ

ይነገር የለም ወይ የባይታዋር ወሬ

 አንድ መሆን ደጉ በትዉልድ ሀገሬ

 ቀድሞ እንደተከላት ጌታ በኤደን ገነት

ያችን የእኔ ተስፋ በአዲስ አበባ አየዎት

 በመኖር አለመኖር በብቻ ስገነት

እንደገዳም ኑሮ የከተማ ባህት

እዚህ ልተግብራት እስኪ አንዴ ልኑራት

 ያችን የእኔን እትብት የትዉልዴን ስምረት

የብቸኝነቴን ጥናት የአርምሞየን ቁመት

......///.....

            17/7/10 

    39

      የዉበት ቱርፋት 



መዉደድ  ድርሻዉ ሰፊ አንችን ያካለለ

በተዋረድ ደርሶ ሁሉን ያማከለ

አንዳችን ስናይሽ ሌላዉ  ይማጠናል

በዉበትሽ ቱረፋት ኪዳሽን ያደርሳል

እንግዲህ ቱረፋት የተስጠሽ ጸዳል

የዉበትሽ ማማ ሀገር ይማርካል

እኔም በተሰጠኝ በአንደኛዉ ብዕሬ

ቃል ከቃል መርጨ ዉብቅኔ ፈጥሬ

 ታሪክሽን ተረኩኝ ለህዝብሽ ለሀገሬ

......///......

                18/7/10 

      40

    በነፋሻዉ ሌሊት



የተነገረሽን የራዕይሽን ዝማሜ

 ወደረ በሌለበት ባሳደረኩት አቅሜ

 አንችን እንደማርያም 21 ምታት

ልደግምሽ ወደድኩኝ በሌሊቱ ብረታት

ንፋስ ያገላታኝ ያዳሬ ብልሃት

በፈረማታዉ  ጠለል ብህሬን ከተብኳት

 አንድ ላንች መስብ አንድ ለነፍሳችን

ሀና ተሳሳምን ቅኝ ነዉ አጥቢያችን

.....///.....

      21/7/10 
 

        41
   

ተስፋየ ባንተ ላይ

         
መደበት መጨፍገግ አግንቶኝ በድንገት

እኔ በብቸታ መነኩሴ በብአት

እንመስል ነበረ ጀግና የምጠብቅ

እረቂቁን ድህነት ህጉን የምናረቅ

ግና ጀግና ይወለዳል እንዳተ ተስፋ ሰጭ

መይሳዉ የሚሉት ስመ ብርቱ አስደጋጭ

ለጥላት መራድን ክፋትን የሚረጭ

ተስፋየም በአንተ ላይ እንደተመሰረተ

 አንድነት መይሳዉ አንድ ናቸዉ ተብሎ በጋድ ተተረተ

                    //////////////
                     2/9/12  


       
42      
 

መንገድህን ግለጥ


መሰዋት ከሆነ መዋ የስጦታ

ለአድራጎት ድጋፍ ለአንቱ ዉለታ

ላደረከዉ ጀብድ ጀግነት እምርታ

ለመቅደላ ሽኝት ለጋፋት ሰላምታ

ለእድገት ቴክኖሎጅ ለጊዜዉ ፍጆታ

መንገድህን ግለጥ ክንድህ ሳይረታ

መይሳዉ ተናገር የአንተን ሚስጥር ዉሎ
  
ልቤ አንተን መሆን ስምህን ከጅሎ
  
በፍቅር በረረ አንድ ሽፍታ አክሎ

የመቅደላን ታሪክ ዉሎዋንም መስሎ

እኔን በመንገድህ በዉበት ደልሎ

በወድነትህ ቃል በፍቅር አታሎ

ሰጠኝ ናፍቆትህ ትዝታህ ስሎ

          ///////////////
           8/27/12   
 
      
  .....  ተፈጸመ .... 


 

No comments:

Post a Comment